Web Toolbar by Wibiya

Follow Us

“መገንጠል ለሚፈልግ ግዜዉ ሲደርስ መገንጠል መብቱ ነዉ” – በረከት ስምኦን.

ኢትዮጵያን ነገስታት መርተዋታል፤ ወታደራዊ አምባገነኖች ጨፍረዉባታል፤ ዛሬ ደግሞ ዘረኛ አምባገነኖች ቁም ስቅሏን እያሳዩዋት ነዉ። እቺን ለአስተዋይ መሪዎች ያልታደለች የአስተዋዮች አገር ዛሬ አለም የሚያዉቃት በድህነት፤ በረሀብና በስደት ነዉ። ድህነት፤ ረሀብና ኋላ ቀርነት ኢትዮጵያ ላይ የተደቀኑ ታላላቅ አደጋዎች ቢሆኑም ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያን ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈራት ድህነትና ረሀብ ሳይሆን ወያኔ በግድ የጫነባት የመገነጣጠል አደጋ ነዉ።

በአባቶቻችን የደም መስዋዕትነት ተከብሮ የኖረዉ የኢትዮጵያ አንድነት የሚያሳስባቸዉ ኢትዮጵያዉያን “መገንጠል” የሚሉትን አደጋ ሲሰሙ ልባቸዉ የሚቀልጠዉ ወያኔ ህግ በመንግስቱ ዉስጥ መገንጠል ይቻላል ብሎ ስለጻፈ ብቻ አይደለም። አያሌ ኢትዮጳያዉያንን የሚያሳስባቸዉና የሚያስፈራቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ቁልፍ ቁልፉን የስልጣን ቦታዎች ቆንጥጠዉ የያዙት ሰዎች የሚናፍቃቸዉ የኢትዮጵያ አንድነት ሳይሆን የኢትዮጵያ መበታተን በመሆኑ ነዉ። ከእነዚህ የኢትዮጵያን ዉድቀትና መበታተን ከሚመኙ ከሀዲ ሰዎች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ በረከት ስምኦን ነዉ።

በረከት ስምኦን የኢትዮጵያን ትልቅነት የሚያቀልሉና የኢትዮጵያን ህዝብ ማንነት የሚያሳንሱ አያሌ አጥንት የሚሰብሩ ንግግሮች ያደረገ እብሪተኛ ሰዉ ነዉ። በረከት እዉነትን ከዉሸት፤ ቁምነገርን ከቧልት አገርን ያክል ትልቅ ነገርና የቤቱን ጓዳ ለይቶ ማየት የማይችል እንኳን ለአገር ስልጣን ለዕቁብ ዳኝነትም የማይመኙት ሰዉ ነዉ። ሆኖም እሱና የደደቢት ጓደኞቹ አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ የስልጣን መያዣ መለኪያዉ ብስለትና አስተዋይነት ሳይሆን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መጥላትና ማጥላላት በመሆኑ በረከት ስምኦን ዛሬም ድረስ እንደጨበጠ የያዘዉን ስልጣን ለመያዝ ችሏል።

ከሰሞኑ ስራ ፈቱ በረከት ስምኦን “የኤርትራ ተቃዋሚዎች አረብኛ ፓልቶክ” በተሰኘ የመወያያ መድረክ ላይ ቀርቦ ቃለመጠይቅ ሰጥቶ ነበር። የዚህ መጣጥፍ ቁምነገር በረከት ስምኦን ቃለመጣይቅ መስጠቱና አለመስጠቱ ላይ አይደለም። ቃለመጠይቅ መስጠትና አለመስጠት የራሱ ጉዳይ ነዉ። ሆኖም ቃለመጠይቁ አገርን ያክል ትልቅ ነገር የሚበክል መርዝ ስለነበረበት ማርከሻ ይሆነዋል በሚል የዚህን እብሪተኛ ሰዉ ቃለመጠይቅ በዚህ ጽሁፍ ለመዳሰስ ተገድደናል።

ጉዳዩ እንደዚህ ነዉ – በቅርቡ በረከት ስምኦን “አረቢክ” የሚባል ፓልቶክ መድረክ  ላይ ቀርቦ ቃለመጠይቅ ሰጥቶ ነበር። ቃለመጠይቁ  የኢትዮጵያ ጉዳይ እጅግ የሚያሳሳብቻዉን እትዮጵያዉያን ቀርቶ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ ታሪካዊ ደባ የፈጸሙትን የህወሀት አባላትን ጭምር አስቆጥቷል።  በረከት ስምኦን በዕለቱ ከተናገራቸዉ ብዙ የክህደትና የጥላቻ ንግግሮች ዉስጥ አንደኛዉ “አንድነትና አንድ አገር የሻዕቢያ መዝሙር ነዉ” የሚል ሲሆን ሌላኛዉ ደግሞ “ኢትዮጵያ ዉስጥ መገንጠል ለሚፈልጉ ግዜዉ ሲደርስ መገንጠል መብታቸዉ ነዉ” የሚል ነበር።

ለመሆኑ በረከት ስምኦን “አንድነትና አንድ አገር” የሻዕቢያ መዝሙር ነዉ ሲል ምን ማለቱ ነዉ? በረከትና የደደቢት ጓደኞቹ ኢትዮጵያን የሚመለከቷት እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ነዉ ወይስ ኢትዮጵያ እነሱ ሲፈልጉ አንድ የምትሆን እነሱ ካልፈለጉ ደግሞ ተገነጣጥላ ብዙ የምትሆን አገር ናት። በረከትና ወያኔ አዲስ አበባ ሲገቡ ኢትዮጵያ ስንት ነበረች ዛሬስ ስንት ናት? መቼም ወያኔና በረከት ስምኦን ሺ ግዜ ቢነገራቸዉ የማይገባቸዉ ጭራሽ ባይነገራቸዉም ቀረብን የማይሉ ግዑዝ ዕቃዎች ሆነዉ ነዉ እንጂ ከአራቱም ማዕዘን ስንቁን ተሸክሞ በእግሩ አድዋ ድረስ የተመመዉ የኢትዮጵያ ህዝብ መንገድ ላይ የዘመረዉ ብቸኛ መዝሙር “አገሬ ኢትዮጵያ” የሚል መዝሙር ነበር።  በረክትና ጓደኞቹ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና የኢትዮጵያ አንደ አገር ላይጥማቸዉ ይችላል፤ ቁጥሩ ከ90 ሚሊዮን ባላይ አንደሆነ የሚገመተዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ለአገሩ አንድነትና ሉዓላዊነት ህይወቱን ለመስጠት የማይሳሳ ህዝብ ነዉ። እዉነትም ሟርተኛዉ በረከት እንደተናገረዉ “አንድነትና አንድ አገር” የሻዕቢያ መዝሙር ከሆነ የእኛ የኢትዮጵያዉያን መዝሙርስ ምን ይሆን?  ወይስ በረከት የሱን መዝሙር እኛም እንድንዘምርለት ይፈልጋል!

ሌላዉ በረከት ስምኦን የተናገረዉና አንድነቱን የሚወድደዉን የኢትዮጵያን ህዝብ እጅግ ያበሳጨዉ ንግግር “ኢትዮጵያ ዉስጥ መገንጠል ለሚፈልጉ ሁሉ ግዜዉ ሲደርስ መገንጠል መብታቸዉ ነዉ” ብሎ የተናገረዉ ንግገር ነዉ። በሚሎዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በየዘመኑ በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ተጠብቆ የኖረዉን የኢትዮጵያን አንድነት በረከት ስምኦን እንደቀላል ነገር  በግዜ ገድቦ ነበር ያስቀመጠዉ። ሁላችንም በግልጽ እንደምናዉቀዉ ይህ የበረከት ስምኦን ንግግር አዲስ አይደለም፤ ወያኔ ከጫካ ጀምሮ የተከተለዉ ፀረ ኢትዮጵያ እስትራቴጂ ነዉ። የወያኔዎች አላማ አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ ተቃዋሚ ሀይሎችን አጥፍቶ ኢትዮጵያን እየዘረፉ መኖር ነዉ። ተቃዋሚዎች አይለዉ የወያኔ ስልጣን አደጋ ላይ ይወድቃል ብለዉ ከሰጉ ደግሞ እነሱ ትግራይን ተቆጣጥረዉ ሌላዉን የኢትዮጵያ ክፍል በታትነዉ መሄድ ነዉ። በረከት ስምኦን በሰጠዉ ቃለ መጠይቅ ላይ “ግዜዉ ሲደርስ” መገነጣጠል ይቻላል ያለዉም ይህንኑ ጫካ ዉስጥ እያሉ ተዋዉለዉ የመጡትን ኢትዮጵያን የማጥፋት ዉል ለመጠቆም ነዉ።

መለስ ዜናዊ በህይወት በነበረበት ወቅት ደጋግሞ አንደተናገረዉም ይሁን ዛሬ በረከት በየፓልቶኩ መድረክ እንደሚለፈልፈዉ እቺ ኢትዮጵያ ተብላና ዘመናትን አቋርጣ እኛጋ የደረሰችዉ የጀግኖች አገር “ግዜዉ ሲደርስ” በትንሹ ከሁለት እስከ ዘጠኝ ትናንሽ አገሮች ልትቆራረስ ትችላለች። ባጠቃላይ እንደነበረከት አባባል ኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰበቿ ደስ ሲላቸዉ የሚተክሏት ሲከፋቸዉ ደግሞ ነቃቅለዉ የሚያፈርሷት የእድር ድንኳን ናት። እንግድህ እነዚህ ናቸዉ የኢትዮጵያን ህዝብ አስተባብረዉ አባይ ወንዝ ላይ ግድብ የሚሰሩት . . . ነገ የማን መሆኑ እንኳን የማይታወቅ ግድብ! እነዚህ የነገይቱ ታላቅ ኢትዮጵያ ራዕይ የሌላቸዉ ከሀዲዎች ናቸዉ በኢትዮጵያ ስም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚበደሩትና በኢትዮጵያ ሰም አለም አቀፍ ዉሎችን የሚፈራረሙት! አቤት እግዚኦ! አቤት ኢትዮጵያ. . . . እቺ ናት የመለስ ራዕይ!

ይህንን “መገንጠል” የሚሉትን በወያኔ ህግ መንግስት ዉስጥ የተቀመጠዉንና እነ በረከት ስምኦን ዛሬም ድረስ የሚያጠነጥኑትን የባለጌ መዝሙር አፋችንን ከፍተን የምንሰማ ከሆነ መናገሻ ከተማችን አዲስ አበባ፤ዉብ ከተሞቻችን አዋሳ፤ ባህርዳር፤ ጂማና ናዝሬት፡ ታሪካዊ ከተሞቻችን አክሱም፤ ላሊበላ፤ ጎንደርና ደብረበርሀን የጀግኖቻችን አጽም ያረፉባቸዉ ቦታዎች አነ መቅደላ፤ መተማ፤አድዋ፤ማይጮዉና ወልወል እንደዚሁም የቡና መሬቶቻችን ዲላ፤ግምቢና አጋሮ እነ በረከት “ግዜዉ ሲደርስ” ያሉት ግዜ ሲደርስ ኢትዮጵያ ከሚባል ታሪካዊ ስም ጋር የነበራቸዉና አሁንም ያላቸዉ የደም፤ የመስዋዕትነትና የአብሮ መኖር ወንድማማችነት ግንኙነት እንዳልነበረ ሊሆን ነዉ ወይም ዛሬ አንድ የሆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የነበረከት ግዜ ሲደርስ “እኛና እነሱ” ልባባል ነዉ።

ዉድ ኢትዮጵያዉያን ይህ እንደ ሰማይ የገዘፈ ጥፋት “ሰዉረነ ከመአቱ ….አድነነ ከጥፋቱ”  ብለን አማትበን የምናልፈዉ ተራ ጥፋት አይደለም። ደግሞም ይህ ግዙፍ ጥፋት የተዶለተዉ በእኛ ዛሬ በህይወት ባለነዉ ኢትዮጵያዉያን ላይ ብቻ አይደለም። ይህ ታሪካዊ ጥፋት እቺን አገር አደራ ጥለዉልን ባለፉት በአባቶቻችን ላይ፤ በእኛ ላይና በመጪዉ ትዉልድ ላይ ሁሉ የተዶለተ ትዉልድን ወደኋላና ወደፊት ያጣቀሰ ጥፋት ነዉ። ሆኖም አባቶቻችን ሐላፊነታቸዉን ተወጥተዉ ስላለፉ መጪዉ ትዉልድ ደግሞ ገና ስላልተወለደ ይህንን ጥፋት ማስቆም ብቻ ሳይሆን የጥፋቱን መሐንዲሶች መደምሰስ የዚህ ትዉልድ ሐላፊነት ነዉ።

በረከትና ጓደኞቹ የአገራችንን ጉደይ “ግዜዉ ሲደርስ” ብለዉ ነግረዉናል። ወገን ግዜዉ ደርሷል. . . ግዜዉ ዛሬ ነዉ! እቺን ከአባቶቻችን በአደራ የተረከብናትን አገር እኛም ለልጆቻችን በአደራ ለማስረከብ የተዘጋጀን ኢትዮጵያዉያን ሁሉ “ነፃነት ወይም ሞት” ብለን የምንነሳበት ቀን ዛሬ ነዉ። እኛ ሞተን ኢትዮጵያን በህይወት ማቆየት ከተሳነን ታሪክና ትዉልድ የሚያስታዉሱን “አደራዉን የበላ ትዉልድ” እያሉ ነዉ። ለአገሩ መሞትን ፈርቶ ይህንን ከሞት በላይ የከፋ ዘለአለማዊ ስም መቀበል የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ደግሞ በታሪካችን አልነበረም፤ ዛሬም የለም  ለወደፊትም አይኖርም።  እንግዲህ የእናት ኢትዮጵያን ትንሳኤ እዉን ለማድረግ ትግሉን የተያያዝነዉ ሁሉ ሞት በሌለበት ትንሳኤ የለምና ለሞትና ለመስዋዕትነት የምንዘጋጅበት ግዜዉ አሁን ነዉ።

ግንቦት 7

17, Novemeber 2012.

0 comments: